የደግነት ጋሻ
በአበበ ከበደ የተተረከ
ሶስት ወንድ ልጆች የነበሩት አንድ ሰው ነበር፡፡ ልጆቹንም በጥሩ ሁኔታ በመንከባከብ መልካም ባህሪይ ይዘው እንዲያድጉ አደረገ፡፡ በዚያን ጊዜ መልካም አዛውንት ሰዎች አሟሟታቸውን መተንበይ ይችሉ ነበርና ይህም አባት የመሞቻው ቀን እየተቃረበ መምጣቱን ባወቀ ጊዜ ሶስቱን ልጆች ጠርቶ ሃብቱን በማካፈል ከብቶቹን፣ መሬቱንና የእንሰት ተክሎቹን ከፋፍሎ ካወረሳቸው በኋላ መርቆ ሸኛቸው፡፡ ለራሱ ያስቀረው ነገር ጋሻውን ብቻ ነበር፡፡
በሲዳማ ባህል ጋሻ በጣም ልዩ ንብረት ነው፡፡ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የቤተሰብ ውርስ ነው፡፡ ነገር ግን ለታላቅ ልጅ ሳይሆን አባትየው ከልጆቹ መሃል ታላቅ ሰው ይሆናል ብሎ ለሚያስበው ሰው ይሰጥ ነበር፡፡ ይህ ሰው ግን ጋሻውን ለየትኛውም ልጅ አልሰጠም፡፡
አባትየውም “ልጆቼ ሆይ! ደግነት በባህላችን ትልቅ ዋጋ አለውና እናንተም አሁን ሄዳችሁ መልካምና ደግ ስራ ሰርታችሁ እንድትመጡ እፈልጋለሁ፡፡ ከዚያም ወደዚህ ተመልሳችሁ የሰራችሁትን መልካም ነገር ትነግሩኛላችሁ፡፡ ከእናንተ ውስጥ የበለጠውን ደግነት ላደረገው ልጄ ይህንን የውርስ ጋሻ እሸልመዋለሁ፡፡” አላቸው፡፡
ልጆቹም ሁሉ ጋሻውን ይፈልጉት ነበርና መልካሙን ነገር ለማድረግ በየፊናቸው ሄዱ፡፡ ከሄዱበትም ሲመለሱ አንደኛው “አባቴ ሆይ! አንድ በጣም ደግ ነገር አድርጌያለሁ፡፡ እንግዲህ አንተ ፍረድ፡፡ አንድ በዳዴ የሚሄድ የነበረ ህጻን ከአንዲት ወንዝ ውስጥ ወድቆ እናቱ በፍርሃትና በድንጋጤ ቆማ ስታየው እኔ ለህይወቴ ሳልሳሳ ወንዙ ውስጥ ዘልዬ ገብቼ ህጻኑን አዳንኩት፡፡” አለ፡፡
አባትየውም “ይህ ደግነት አይባልም፡፡ ይህ ሰው በመሆንህ ብቻ የምታደርገው ሰብአዊነት ነው፡፡ ህጻንንም ማዳን ያው ነው፡፡ ይህን ማንም ሊያደርገው ይችላል፡፡” አለ፡፡
ሁለተኛውም ልጅ “አባቴ ሆይ! አንድ ብቸኛ መንገደኛ በመንገዱ ላይ ሳለ “እባክህ ገንዘቤን ጠብቅልኝ” ብሎ 100 ከብር የተሰሩ የገንዘብ ቅጠሎችን ሰጥቶኝ ሄደ፡፡ ያንን ሁሉ ገንዘብ መስረቅ ስችል ጠብቄለት ሲመለስ 100 ዶላሩን ሰጥቸዋለሁ፡፡ እርሱም 10 የብር ቅጠሎችን ሊሰጠኝ ቢፈልግም ‘አይሆንም፣ ይህ ያንተ ገንዘብ ነው፡፡ እኔ ጠበኩልህ እንጂ ምንም ስላላደረኩልህ ምንም አይነት ሽልማት አልቀበልህም፡፡’ አልኩት፡፡ ይህ ደግነት አይደለም?” አለው፡፡
አዛውንቱም አባት “አይደለም ልጄ! ይህ የሚያሳየው አንተ የገንዘብ ፍቅር እንደሌለህ ነው፡፡ ይህ በርግጥ ጥሩ ባህሪይ ነው፡፡ ነገር ግን ደግነት አይደለም፡፡” አለው፡፡
ካያም የተባለው ሶስተኛው ልጁ “እሺ፣ እኔ ደግሞ ያደረኩትን ልንገራችሁ፡፡ በመንገድ ላይ እየሄድኩ ሳለ በድንገት ቀንደኛ ጠላታችንና ለዘመናት ስንጣላው የነበረውን ሰው በድንገት አገኘሁት፡፡ ከገደል አፋፍ ላይ ተኝቶ ነበርና ሄጄ ገፍትሬ ገደሉ ውስጥ ልጥለው ስችል ወይም ሄጄ ስቀሰቅሰው ቀና ብሎ ሲያየኝ ከቤተሰቤ ጋር ለረጅም ጊዜ ሲናቆር መኖሩን ስለሚያውቅ ለመዞር ሲገላበጥ ገደሉ ውስጥ ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ቀስ ብዬ ቀስቅሼው ወደ ደልዳላ ቦታ በመውሰድ ያለ ስጋት እንዲተኛ ካደረኩት በኋላ ትቼው ሄጃለሁ፡፡” አለ፡፡
አባትየውም “አዎ፣ ልጄ ይህ ነው እውነተኛ ደግነት፡፡ እርሱ ያንተ ጠላት ብቻ ሳይሆን የቤተሰቡ በሙሉ ጠላት ነው፡፡ ነገር ግን አንተ ህይወቱን አድነኸዋልና ጋሻውን የምሰጠው ላንተ ነው፡፡” አለው፡፡
የታሪኩም መልዕክት “ጠላቶችህን በበቀል አትፈልጋቸው፡፡” የሚል ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|