ዔሊ ሽፋኗን እንዴት እንዳገኘች
በይሳቅ አልዳዴ የተተረከ
ይህ ታሪክ ስለዘላለማዊው አምላክ፣ የሰማይና ምድር ፈጣሪ ጌታ፣ የፍጥረታቱ ሁሉ ፀሎት ሁልጊዜ ወደ እርሱ የሚደርስበትና የተጨቆኑትም እንዳይጨቆኑ የሚያደርግበትን ሁኔታ የሚነግረንና አምላክ ፍትሃዊ ጌታመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
አንዲት ኤሊ የምትባል ፍጡር ነበረች፡፡ ይህች ኤሊ በጣም ደካማና እንዳሁኑ ሽፋን ያልነበራት እንስሳ ነበረች፡፡ እንደ እንሽላሊትና እንደ እንቁራሪት ቀስ ብላ የምትራመድ ደካማ እንቁራሪት ነበረች፡፡
ታዲያ ይህች ኤሊ ስትኖር፣ ስትኖር አንድ ቀን በፊት አብረዋት በሰላም ይኖሩ የነበሩት እንስሳቱ ተንኮል ያሴሩባት ጀመር፡፡ የጫካው እንስሳት ሁሉ፣ በሰማይ የሚበሩ አእዋፋትን ጨምሮ ሁሉም እንስሳት ተንኮል አሲረው “በነገራችን ላይ፣ይህች ኤሊ ምንም ዘመድ የላትም፡፡ ምንም ሁነኛ ደጋፊና የሚከላከልላት ስለሌለ ለምን ሁላችንም ተሰባስበን በጣጥሰን አንበላትም?” ይባባሉ ጀመር፡፡
በዚህ ሁኔታ ከተመካከሩ በኋላ ቀኑን ሙሉ ሲወያዩበት ውለው ሌሊቱንም ሲወያዩበት አደሩ፡፡
ከእንስሳቱም መሃከል አንበሶች፣ ነብሮች፣ ጅቦች፣ ትንንሽና ትልልቅ አእዋፋት፣ የሰማይ ንስር፣ ትልቅ ንስርና አሳ በል ጭልፊትም ነበሩበት፡፡ ሁሉም የአእዋፍ ዘርና እንስሳቱ በሙሉ ተባበሩባት፡፡ ከውይይታቸውም በኋላ በማግስቱ ልክ በ4 ሠአት ለመገናኘትና ማንም እንዳይቀር ውሳኔ አስተላለፉ፡፡
“እናም ኤሊዋ ምንም አቅም ስለሌላት እንበላታለን፡፡” በማለት ተስማሙ፡፡
በዚህ ከተስማሙ በኋላ በመጨረሻ በነገው ድግስ ወስነው ወደየቤታቸው ተመለሱ፡፡
በዚያን እለት ማታ አንዲት የኤሊዋ ጓደኛ የነበረችና በስብሰባው ላይ ተካፍላ የነበረች አንዲት እንስት እንስሳ ሌሊቱን ሙሉ ተጉዛ ወደ ኤሊዋ ዘንድ በመሄድ “ውዷ ኤሊ ሆይ፣ ምን እያደረግሽ ነው? አንድ አደጋ መጥቷል፡፡ ፍጥረታቱ ሁሉ ዛሬ ተሰብስበው ነገ በ4 ሰአት አንቺን ሊበሉሽ ተስማምተው ወስነዋል፡፡ በጣጥሰው ሊጥሉሽ ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል፡፡ እርስ በርስም ተመካክረዋል፡፡” ብላ ነገረቻት፡፡ ኤሊዋም “እንደዚያ ነው?” አለች፡፡
“አዎ”
“እኔን ሊበሉኝ?”
“አዎ”
በዚህ ጊዜ ኤሊዋ ማልቀስ ጀመረች፡፡ “እንግዲህ ማን ሊያድነኝ ይችላል? ከዚህ ስቃይ ማንስ ሊታደገኝ ይችላል? ሲጀምር ምንም መከላከያ የለኝም፡፡ ልብሶችም የሉኝም፡፡ አቅምም የለኝም፡፡ እዚህ ግባ የሚባልም ጡንቻ የለኝም፡፡ ታዲያ ማነው የሚያድነኝ?” በማለት ምርር ብላ ማልቀሷን ቀጠለች፡፡ ከዚያም ስለሴራው የነገረቻትን የቀድሞ ጓደኛዋን “አዳምጪ” አለቻት፡፡
ጓደኛዋም “እሺ” አለቻት፡፡
“ለመሆኑ ይህንን ሁሉ ሴራ ያሴሩብኝ እነማን ናቸው?”
“አንበሳ፣ ነብር፣ ዝንጀሮና ሁሉም አእዋፋት በሙሉ!”
ከዚያም ኤሊዋ ብዙ ካሰበች በኋላ “የሰማዩም ንስር አብሮ ነበር፡፡” አለቻት፡፡
ኤሊዋም በመገረም “እርሷም እኔን ልትበላኝ አብራ አሴረች?” ብላ ጠየቀች፡፡ በመጨረሻም “ሌላስ ማን ነበር?” ብላ ስትጠይቅ ነጋሪዋ “አንበሳ፣ጅብና ሌሎችም ሁሉ ነበሩ፡፡” ብላ ነገረቻት፡፡
ከዚያም ኤሊዋ “እሺ ግን አንድ ጥያቄ ብቻ ልጠይቅሽ፡፡ አምላክ በሴራው ላይ ተካፍሏል? ሊበሉኝ ካሴሩት ሁሉ መሃል እግዜር ነበር?” ብላ ጠየቀቻት፡፡
“በርግጥ እግዜር በሴራው አልተሳተፈም፡፡”
“እግዜር እዚያ አልነበረም?”
“አልነበረም፡፡”
“እንግዲያው እግዜር ከሌለበት ምን እንደምሆን እግዜር ያውቃል፡፡ እሱም ያድነኛል፡፡” ብላ ኤሊዋ ተናገረች፡፡ ከዚህ በኋላ በሚቀጥለው ቀን እንስሳቱ ሁሉ በተቀጣጠሩበትና ኤሊዋን ሊበሏት በቆረጡበት ተገናኝተው ሊፈልጓት አብረው መጡ፡፡ ነገር ግን ቢፈልጓት፣ ቢፈልጓት ያጧታል፡፡
ከዚያም “ኧረ ከዚህ ድንጋይ አጠገብ ነበረች!” አሉ፡፡
ከዚያም ፍለጋቸውን በመቀጠል ድንጋዩ አጠገብም ቆመው ቢያይዋት ሊያገኟት አልቻሉም፡፡ አምላክ ታዲያ የዚያን እለት ሌሊቱን ድንጋይ አልብሷት አድሮ ነበር፡፡ እንስሳቱ ግን ድንጋዩዋ ላይ ቆመው ይፈልጓት ነበር፡፡
እየፈለጓትም “የታለች?” እያሉ ይጠይቁ ነበር፡፡
ከዚያ እለት ጀምሮ ታዲያ ፈጣሪ ኤሊን ድንጋይ አልብሷት ሊበሏት ካሴሩባት እንስሳት በሙሉ በድንጋይ ሸፍኖ አድኗታል፡፡
አንድ ሰው ሌላውን ሊያጠቃ ሲነሳ ወይም አንዱ የሌላውን ደካማነትና አቅም አልባነት ተመልከቶና የሚቆምለት ሰው የለም ብሎ ሊጎዳው ቢነሳ የዘለዓለሙ አምላክና የአለሙ ሁሉ ፈጣሪ ከጎኑ ይቆማል፡፡ በዳዩ ይህንን ሊያውቅ ይገባል፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ወደሚቀጥለው > |
---|